የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሜዲስን ተማሪዎች ነጭ ጋዎን የመልበስ ቀን አከበሩ።

ህዳር 3/2016
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲቲዩት 4ኛ ዓመት የሜዲስን ተማሪዎችን ነጭ ጋዎን(ካባ) የመልበስ ቀንነ በደማቅ ሁኔታ ያከበሩ ሲሆን ተማሪዎቹ ከpre-clinical መማር ማስተማር ወደ clinical መማር ማስተማር የተሸጋገሩበትን 4ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው።  በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማን ጨምሮ የኢንስቲቲዩቱ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል::
በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የህክምና  ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሐሰን ቦኩ የህክምና ትምህርት ከፍተኛ የሆነ የግል ጥረት እንደሚፈልግ በመግለፅ ተማሪዎች የሚኖራቸውን ሙያ ለማሳደግ እና ጥሩ ሀኪም ሆኖ ለመገኘት መጣር እንዳለባቸው አሳስበዋል:: 
የጤና እንስቲቲዩት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሳፋዪ ኤሌማ በበኩላቸው ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተማሪዎች ከትልልቅ የህክምና መፅሐፍቶችና ከታካሚዎች  ጋር የምትገናኙበት ወቅት ስለሆነ ሙያው የሚፈልገውን ትዕግስት እና የጊዜ አጠቃቀም በማሳደግ በቁርጠኝነት መስራት አለባችሁ ብለዋል:: በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ከሰው ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የስራ ሂደት ውስጥ የምትገቡ በመሆናችሁ ጥሩ ተመራማሪ እና ባለሙያ መሆን ይጠበቅባችኋል ብለዋል:: ከመማር ማስተማር አንፃርም ከሜዲስን ተምሪዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ፕሬዝዳንቱ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለሃያ ስምንት (28) አራተኛ ዓመት የሜዲስን ተማሪዎች ነጭ ጋዎን የማልበስ ፕሮግራምም ተካሂዷል።