የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ውይይት አደረገ

ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም
የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ውይይት አደረገ። በውይይቱ የሆስፒታሉ ቦርድ አደረጃጀት፣የሆስፒታሉ ቦርድ አመራር ሀላፊነት፣ ክትትል እና ምዘና እንዲሁም አጠቃላይ የስራ ሂደት በስፋት ተብራርቷል ።
የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ከማሻሻል አንፃር የሆስፒታሉ ቦርድ ሊኖረው ስለሚገባው ሀላፊነትም ሰፊ ውይይት ተካሂዷል ።
የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢና የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ረ/ፕ ገመዳ ኦዶ የሆስፒታሉ የቦርድ አመራር ፤ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ በመስራት የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ የጋራ ሀላፊነት መሆኑን በመጠቆም የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ አመራር ተገቢውን የድጋፍ እና ክትትል ስራ ማከናወን እንዳለበት ገልፀዋል።
ከበርካታ ችግሮች ጋር በመሆን ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ የሆስፒታሉ አጠቃላይ ሠራተኞች ምስጋና ያቀረቡት ረ/ፕሮፌሰሩ የህክምናውን ሂደት ይበልጥ ለማደራጀትና ለማዘመን እንዲሁም የሰው ሀይል እና የቁሳቅስ እጥረት በሆስፒታሉ እንዳይታይ ለማድረግ ቦርዱ መሠረታዊ ሀላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል።
የማስተማሪያ ሆስፒታሉን የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ጤና ኢንስቲትዩት ዲን መ/ር ታከለ ኡቱራ በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ ውስንነቶችና ጠንካራ ጎኖችን በሪፓርቱ ዳሰዋል። በተለይም ሆስፒታሉ በዩኒቨርሲቲው ስር ከሆነ ጀምሮ የስፔሻላይዝድ ባለሙያ ቁጥር መጨመር ፣መድሀኒት የመግዛት አቅም ማሳደግ፣የህክምና ማሽኖች በከፊል ማሟላት በሆስፒታሉ የሚታዩ ለውጦች መሆናቸውን የገለፁት መ/ር ታከለ የመኝታ ክፍሎች ከበቂ በታች መሆን፣በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋል የመድሀኒት ችግር፣የበጀት እጥረትእና የመሰረተ ልማት አለመሟላት ሆስፒታሉ ለሚሰጠው የህክምና ሂደት እንቅፋት መሆናቸውን በሪፖርቱ አመላክተዋል።
መ/ር ታከለ ኡቱራ አክለውም የ2015 በጀት ዓመት የሆስፒታሉን እቅድ ያቀረቡ ሲሆን በ2015 ዓ/ም የማስተማሪያ ሆስፒታሉን ወደ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል።
የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ እና በሆስፒታሉ የሚታዩትን ውስንነቶች ለመሙላት ፤ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት የህክምና ሂደቱን ለማዘመን እንደሚሰራም በውይይቱ ተጠቁሟል።
ለላቀ ለውጥ እንተጋለን!
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ