ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ

መጋቢት 13/2018 ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ

ዩኒቨርሲቲው ከ15ኛ ዙር ተማሪዎች ምርቃት ጎን ለጎን የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የተቀላጠፈ እንዲሆን በማድረግና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወቱ እንዲሁም የማህብረሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ታስበው የተገነቡ ሦስት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር እና ማህብረሰብ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ሠራዊት ሃንዲሶ እና ለሎችም የትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር አካላት በተገኙበት አስመርቋል።

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል መንግስት ዲጅታል 2030 ያስቀመጠውን ስትራቴጅ የሚደግፍ፣ዘመናዊ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓትን ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወትና በአጠቃላይ በቀጣይ የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥና የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን ወረቀት አልባ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያለውና ከ280 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበት ሞጁላር ዘመናዊ የዳታ ሴንተር ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ተደርጓል።

በተጨማሪም ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ከተደረጉት ፕሮጀክቶች መካከል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርት አሰጣጥ በተሻለ መልኩ እንዲሆን በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ በውስጡ 46 የመማሪያ ክፍሎች 16 ለተለያዩ ሥራዎች የሚያገልግሉ ቢሮዎችን እና ሁለት ትላልቅ ዲጂታል ላይብረሪዎችን ለማደራጀት ታስበው የተገነቡ አምስት ብሎክ ህንፃዎችም ተመርቋል።

ለመምህራን ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠርና የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የተገነቡ እና ለ133 አባወራዎች የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችም ተመርቋል።