ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ለ15ኛ ጊዜ 1266 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል።

መጋቢት 13/2018

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ኮሌጆች ሲያሰለጥናቸው የቆየውን ተማሪዎች የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የዞንና ከተማ መስተዳድር አመራሮች ፣የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላት ፣አባ ገዳዎች፣የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የተማሪ ወላጆች በተገኙበት በመጀመሪያ ድግሪ 992 ተማሪዎች በሁለተኛ ዲግሪ 269 በሦስተኛ ድግሪ ( Ph.D) 5 ተማሪዎችን በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።

በምረቃ በዓሉ ላይ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ንግግራቸውን የጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተመስገን ደበሎ ትምህርት የአመለካከት፣የእውቀት እና የክህሎት በመለወጥ ለሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሚያዘጋጅ መሣሪያ መሆኑን እና በዚሁ መልኩ የተለወጠ ዜጋ ለቤተሰቡም ሆነ ለሀገር ለውጥ ይተጋል ሲሉ ገልፀዋል።

አያይዘውም ዶ/ር ተመስገን ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀት መሠረት ሙያቸውን በማክበር ከሙስና እና ብልሹ አሠራሮች ራሳቸውን በመግታት በትህትናና እራስን በመግዛት ለኢትዮጵያ ከፍታና ብልጽግና የቀሰሙትን እውቀት እንዲያውሉ የአደራ መልዕክት አስተላልፏል።

ዶ/ር ተመስገን በመጨረሻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ በቀዳሚነት በተሰጡት ተልዕኮች ዙሪያ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት እና መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚል እያካሄደ ባለው የሪፎርም ሥራዎች መሠረት ዩኒቨርሲቲውም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ያለበትን አግባብ ጭምር በመድረኩ ላይ ገለፃ አድርጓል።

በተጨማሪም ለተመራቂ ተማሪዎች የሥራ መመሪያ የሰጡት በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር እና ማህብረሰብ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ሠራዊት ሃንዲሶ የአንድ ሀገርም ሆነ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውጤታማነት የሚለካው በንድፈ ሀሳብና በተግባር በሚሰጡ ትምህርቶች ምዘና በሚገኘው ነጥብ ብቻ ሳይሆን የተማሩትን ወደ ተግባር በመለወጥ በሚያሳዩት ችግር ፈቺ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎችም በዚሁ አግባብ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ ጠይቋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ሠራዊት አክለውም ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች እየሠራ መሆኑን በሪፎርሙ መሠረትም በቀጣይም ዩኒቨርሲቲውን መመሪያ በሚፈቅደው ልክ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ምርምር፣ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህብረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገበየሁ አሻግሬ እና በዩኒቨርስቲው ሪጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን ፈይሳ ጋባዥነት ተመራቂዎች በክብር እንግዶች ፊት ቀርበው የተመረቁ ሲሆን በውጤታቸው ብልጫ ላመጡ ተማሪዎችም የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።