በቡሌ ሆራ  ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲው የአሥር ዓመት የሥራ  ዕቅድ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

25/12/2014
የቡሌ ሆራ  ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታምሩ አኖሌ ከዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላት ጋር በዩኒቨርሲቲው የአሥር ዓመት የሥራ  ዕቅድ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ፡፡ 
በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶችን  ጨምሮ የካውንስል አባላቶች ተገኝተዋል፡፡ ከመማር ማስተማር፣ ከምርምር ፣ ከማህበረሰብ አገልግሎት ፣ ከኢንዱስትሪ ትሥሥር  እና ከአጠቃላይ ተቋማዊ የሥራ ትግበራ አንጻር ከ2010 እሰከ 2014 ዓ.ም ድረስ የዩኒቨርሲቲው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በውይይቱ የቀረበ ሲሆን ከ2015 እሰከ 2024ዓ.ም የዩኒቨርሲቲውን የልህቀት ደረጃ ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀው የተቋሙ ዕቅድም ለካውንስል አበላቱ ቀርቧል፡፡ 
ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ደረጃውን ለማሳደግ 2015-2024 ዓ.ም ድረስ የነደፈው እቅድ ዘጠኝ ግቦች እና ሰባ ሁለት እስትራቴጂክ ዓላማዎች ያሉት ሲሆን የመማር ማስተማር፣የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ጥራት ባለው መልኩ ለመከወን እና የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት አቅጣጫዎች ከግብ ለማድረስ የታሰበ እንደሆነም በውይይቱ ተብራርቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደ/ር ታምሩ አኖሌ የዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት እቅድ ከተቋሙ የትኩረት አቅጣጫዎች   ጋር የተጣጣመ መሆኑን በመጠቆም ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ስራዎች ከዩኒቨርሲቲው ግብ እና ከእስትራቴጂክ ዓላማዎች አንፃር ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ በተለይም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲን ወደ ራስ ገዝነት ሊያሳድጉ የሚችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት፣ ከዩኒቨርሲቲው የትኩረት አቅጣጫ ጋር ተመጋጋቢ የሆኑ ፕሮግራሞችን በመክፈትና በማሳገግ ዩኒቨርሲቲው ከምደባ ወደ ቅበላ እንዲያድግ ማድረግ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ በአጽንኦት አስረድተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት ግቦች፣ስትራቴጂክ ዓላማዎች ፣የትግበራ ስልቶች እና የትኩረት አቅጣጫዎች በውይይቱ በስፋት የቀረቡ ሲሆን የካውንስል አባላቱም ተዘጋጅቶ በቀረበው እቅድ ላይ ሀሳብ እና አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡
በውይይቱ የቀረበው የ10 ዓመት ዕቅድ ከካውንስል ዓባላቱ የቀረቡ ሳይንሳዊ ጥቆማዎችን በማቀናጀት ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ለባለድረሻ አካላት እንደሚቀርብ ተገልጿል ፡፡
ለላቀ ለውጥ እንተጋለን!
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ