በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት የ5ኛ ዓመት የክሊኒካል ፋርማሲ ተማሪዎች የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎችን አከናወኑ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ህዳር 26/2017 ዓ.ም (BHU)
የኢንስቲትዩቱ 5ኛ ዓመት የክሊኒካል ፋርማሲ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዉ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህብረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ወራት ወደ ማህብረሰቡ በመዉረድ የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎችን በማከናወን አፈፃፀሙን በዛሬዉ ዕለት የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፤መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት ገምግሟል፡፡
በዕለቱም በም/ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኢንስቲትዩቱ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሳፋይ ኤለማ ኢንስቲትዩቱ በጤና ጥበቃ በኩል ተቀርጾ የመጡ የበጎ አድራጎት ፓኬጅ ሥራዎችንም ሆነ ኢንስቲትዩቱ በራሱ አቅዶ ማህብረሰቡን በጤናዉ ረገድ ልጠቅሙ የሚችሉ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ የቆዬ መሆኑን ተናግሯል፡፡
አያይዘዉም ዶ/ር ሳፋይ በአሁኑ ሰዓትም ተማሪዎች ወደ ማህብረሰቡ በመዉረድ ያከናወኑት የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተማሪዎች ተመርቀዉ ወደ ማህብረሰቡ ሲመደቡ ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን አቅደዉ የመሥራት አቅምን ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀ ስለመሆኑ በመናገር ላበረከቱት አስተዋጾም በኢንስቲትዩቱ ስም ምስጋና አቅርቧል፡፡
በሌላ መልኩ መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ቺፍ ዳይሬክተር ቦኩ ሎኮ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር በተለያዩ ሙያዎች እየሰለጠኑ ያሉ ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ በተጨማሪ በተግባር ተለማምደዉ ወደ ማህብረሰቡ እንዲሄዱ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸዉ ያነሱ ሲሆን የክሊኒካል ፋርማሲ ተማሪዎች ለሁለት ወራት የተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎችን ባከናወኑበት ወቅት የተለያዩ የድጋፍ ስልቶችን በመቀየስ እንዴት ማህብረሰቡን መርዳት እንደሚችሉና ለሚገጥማቸዉ ችግርም እንዴት መፍተሄ ማበጀት እንደሚችሉ ልምድ የቀሰሙበት መሆኑን አስረድቷል፡፡
ተማሪዎቹም በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለዉ በቡሌ ሆራ ከተማ በተለያዩ ቀበሌዎችና በበሪሶ ዱካሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያከናወኑትን ጤና ነክ በጎ አድራጎት ሥራዎችን በተወካዮቻቸዉ አማካይነት አቅርበዉ ዉይይት ከተደረገ በኋላ የምስጋና መስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓትም ተከናዉኗል፡፡