በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ``Cure Blindness``ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በዘመቻ መልክ እየተሰጠ ይገኛል።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም

በሀገራችን በአይን ህክምና ዙሪያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሚሠሩት ግብረሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ``Cure blindness project``ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፍጠር ለበርካታ ዞሮች ከክፍያ ነፃ የሆነ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ከመስጠቱም በላይ በርካታ የህክምና መሣሪያዎችን ጭምር ለግሷል።

በመሆኑም በተመሳሳይ መልኩ ከድርጅቱ ጋር በመተባበር ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከሐምሌ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአይን ህክምና አገልግሎት በዘመቻ መልክ በማስተማሪያ ሆስፒታሉ እየተሰጠ ይገኛል።

አጠቃላይ የተጀመረውን የአይን ህክምና ዘመቻ ሥራ በሚመለከት መግለጫ የሰጡት የማስተማሪያ ሆስፒታሉ የአይን ህክምና ስፔሻልስቲ ዶ/ር አያኖ ቢያሳዝን ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጋር ትብብር በመፍጠር በጤናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎች በተደጋጋሚ መሠራታቸውን ገልፀው በአሁኑ ሰዓት በአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ዙሪያ የተጀመረው ሥራም ድርጅቱ በገባው ውል መሠረት የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለመስጠት እንዲያስችል ከምዕራብ ጉጂ ዞንም አልፎ በአጎራባች ዞኖች ጭምር በመገኘት ለበርካታ ሣምንታት አስፈላጊው የቅስቀሳ ሥራ መሠራቱን አስረድቷል።

አያይዘው ዶ/ር አያኖ ቢያሳዝን ለአምስት ቀናት በሚቆይ ዘመቻ ሥራ ለ500 ግለሰቦች አገልግሎቱን ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን፣ለህክምና አገልግሎቱ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ታካሚዎች የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ የምግብና የመኝታ አገልግሎት ድርጅቱ መቻሉ የገለፁ ሲሆን ከህክምና አገልግሎት በኃላም ለሁለት ወራት ያክል ክትትል የሚደረግላቸው መሆኑንና የአይን መነጽር ጭምር በነፃ የሚቀርብላቸው ስለመሆኑ ገልፀዋል።